የዙራሙሪ መጽሄት የእንግዳ አምድ አንባቢዎቻችን እነሆ በዚህ የአከባቢ ህትመት እትማችን በአንድ ወቅትከኦሮሚያ ክልል ወደ አዊ ብሔ/አስ ከቤተሰቦች ጋር በመምጣት በንግድ ስራ በመሰማራት ስኬታማ ከሆነው ከአቶ ይስማው አለማየሁ ጋር ቆይታ አድርገናል መልካም ንባብ፡፡
ዙራሙሪ ፡- የትውልድ ቦታ እና እድሜ ?
አቶ ይስማው፡- ዕድሜየ 40 ሲሆን የተወለድኩበት ኦሮሚያ ክልል ወለጋ ክፈለ ሀገር ጊምቢ
ከተማ ነው፡፡
ዙራሙሪ፡- የትምህርት ደረጃህ ? የምትኖርበት አካባቢ ?
አቶ ይስማው፡- እስከ 10ኛ ክፍል ዘልቄለሁ፡፡በእንጅባራ ከተማ ነው የምኖረው፡፡
ዙራሙሪ፡- እንዴት ወደ አማራ ክልል አዊ ብሔ/አስ መምጣት ቻልክ ?
አቶ ይስማው፡- ተወልጄ ያደኩት ጊምቢ ከተማ ሲሆን በ1988 ዓ.ም በወቅቱ በነበረው የፖለቲካ አለመረጋጋት ተፈናቅለን ወደ ጎጃም መምጣት ችለናል፡፡ወደ ጎጃም የመጣሁትከእናት አባቴ እንዲሁም ከእህት ወንድሞቼ ጋር ነው፡፡
ዙራሙሪ፡- ለቤተሰብ ስንተኛ ልጅ ነህ ? አዊ ብሔ/አስ አዘና ከተማ ስትገቡ ምን ይዛችሁ ነበር የመጣችሁት ?በምን ስራሰ ቤተሰቦችህ ተሰማሩ ?
አቶ ይስማው፡- ለቤተሰቦቼ 3ተኛ ልጅ ስሆን ምንም አይነት ሀብትና ንብረት ይዘን አልመጣንም ፡፡ሀብታችንና ንብረታችን በግርግሩ ምክንያት እዛው ነበር ትተን የመጣነው፡፡
አባቴ በገምቢ ከተማ ነጋዴ ሰለነበረ ወደ አዊ ብሔ/አስ ስንመጣም ንግድ መሞከር ጀመረ፡፡በ1990 ከ10ኛ ክፍል ላይ አቋርጨ ከሀብታሞች ብር በመቀበል እሁዲት ሚዛን ዘርግቼ ጤፍ፣ሰሊጥ፣በቆሎበመግዛት መልሼ ለሀብታሞች በማስረከብ ጀመርኩኝ ፡፡በዚያን ግዜ እድሜየ 20 ሲሆን ምንም ነገር ያልነበረን በመሆኑ ቤተሰቦቼን እና እኔን በጀመርኩት ችርቻሮ አስተዳደር እና ተናናሾቼን አስተምር ነበር፡፡
አቶ ይስማው
ዙራሙሪ፡- ወደ አዊ ብሔ/አስ ስትመጡ እንዴት ነበርህዝቡ የተቀበላችሁ ?
አቶ ይስማው፡- በአዊ ብሔ/አስ ሁሉም ብሔረሰቦች የሚኖርበት ስትሆን እኛንም ያለምንም
ችግር ተቀብለውናል ፡፡አዊ ብሔ/አስ በአብሮነት በመኖር ፣ለኑሮ ተስማሚ ፣ሰው የሚከበርበት ውብ አካባቢ ነው፡፡
ዙራሙሪ፡- ወደ እርሻ ኢንበስትመንት
እንዴት መሰማራት ቻልክ ?
አቶ ይስማው፡- በንግድ ስራ እየተጠናከርኩ ስመጣ በ1997 ዓ.ም አንድ አስመጪና ላኪ ደንበኛችን እንድ አይሱዝ ሙሉ ሰሊጥ ይዞብኝ ጠፋ፡፡በዚህ ጊዜ ሙሉ በሙሉ ወረቴን ይዞ በመጥፋቱ የከሰርኩበት ዘመን ነበር፡፡ምንም ባልነበረኝ በዚህ ወቅት ግንቦት ወር ላይ በማህበር እርሻ መንግስት ፈቀደልን፡፡ እርሻው 4 ሁነን እንድናርስበት 83 ሄ/ር መሬት የተፈቀደልን ሲሆን ከእኔ ዘንድ ምንም አይነት ገንዘብ አለመኖሩን አውቀው መሬቱን መከፋፈል አለብን ብለው ወሰኑ፡፡ምንም እንኳህጉ ባይፈቅደውም መሬት ተከፋፍለን እርሻ ጀመርነ፡፡ እነሱ 10 ዕቃ በሬ ሲደርሱ እኔ የሰው ፍቅር እና እምነት ስለነበረኝ 5 ዕቃ በሬ ማረስ ቻልኩ፡፡በ1999 ዓ.ም እነሱ በበሬ ሲያርሱ እኔ በትራክተር በማረስ እየተጠናከርኩ መጣሁ፡፡
ዙራሙሪ፡- መቼ ነበር በጋር በማርስ አባይጠጆ እርሻ ልማት የመሰረታችሁ ?
አቶ ይስማው፡- በ2000 ዓ.ም ከአንድ አባላችን በስተቀር 3ሁነን 83 ሄ/ር መሬት ላይ በጋራ ሰሊጥ፣ በርበሬ ፣በቆሎ እና ማሾ ማምረት ችለናል፡፡
እርሻችን በረሃ አካባቢ እና የሰጡትን ሁሉ የሚያመርት በመሆኑ ምርታማነትን ማሳደግ በመቻላችን ተጠቃሚ ሁነናል፡፡
ዙራሙሪ፡- በሄክታር ምን ያህል ምርት ታገኛላችሁ ?
አቶ ይስማው፡- አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ተጠቃሚ በመሆናችን በቆሎ 80 ኩንታል እና በርበሬ እስከ 30 ኩንታል እናገኛለን ፡፡
የአቶ ይስማው መኖሪያ ቤት
ዙራሙሪ፡- በጋራ መስራት ያለው ጠቀሜታ ?
አቶ ይስማው፡- በጋራ መስራት ምርታማነትን ማሳደግ ከመቻሉም በተጨማሪም በጋራ ለማደግ ያስችላል፡፡ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው፡፡
ዙራሙሪ፡- አባይ ጠጆ እርሻ ልማት አሁን ላለህበት ስኬትህ ምን ድርሻ ነበረው ?
አቶ ይስማው፡- ለኑሮየ መቀየር እርሻው ባለውለታየ ነው፡፡
ዙራሙሪ፡- መቼ ነበር ወደ እንጅባራ ከተማ የገባኸው ?ወደ ከተማ የመግባት ምክንያትስ?
አቶ ይስማው፡- የዕድሜየን ግማሽ በረሃ ነበር የኖሩኩት፡፡እሁዲት 3 ልጆችን ወልጀ ሀብት ንብረት ያፈራሁበት አካባቢ ሲሆን በበረሀ ያፈራሁትን ሀብት በብሔ/አስ እንጅባራ ከተማ ኢንቨስት ፍብሪካ ለመገንባት ዕቅድ ይጄ ከ 5 ዓመት በፊት ከተማ ገብቻለሁ፡፡
ዙራሙሪ፡- በብሔ/አስተዳደሩ ፍብሪካ በመገንባት በቅድሚያ ወደ ስራ የገባህም አንተነህ ይባላል ?
አቶ ይስማው፡- እውነት ነው 5ሺ ካ/ሜ መሬት መንግስት ባመቻቸልኝ በከተማው ስንዴ የዱቄት ፋብሪካ ግንባታ በጀመርኩት በአንድ አመት ተኩል ውስጥ ማምረት ችያለሁ፡፡
ዙራሙሪ ፡- በምን ያህል ካፒታል ፋብሪካው ተገነባ ?
አቶ ይስማው፡- ዘንገና ሃይቅ የዱቄት ፋብሪካ በ20 ሚሊዮን ብር ካፒታል የተቋቋመ ሲሆን በቀን 620 ኩንታል የስንዴ ዱቄት መፍጨት ይችላል፡፡
ዙራሙሪ፡- በፋብሪካው የስራ ዕድል ፈጠራው እና ምን ያህል ደመወዝ ይከፈላቸዋል ?
አቶ ይስማው፡- 18 ቋሚ ሰራተኞችን ፋብሪካው ይዟል፡፡ ከቴክኒክ ሙያ የሰለጠኑ ፣የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሩቃን እና ውዛደሮችን ያካተተ ሲሆን 1000 – 9ሺህ ብር በወር ይከፈላቸዋል፡፡
ዙራሙሪ ፡- የገበያ ትስስሩ እንዲሁም የመንግስት ድጋፍ ምን ይመስላል ?
አቶ ይስማው፡- የመብራት መቆራረጥ ችግር በስፋት በመኖሩ ምክንያት ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ማምረት ባለመቻሉ እንጂ እስከ አሁን የገበያ ችግር የለብኝም፡፡ መንግስት በየወሩ 3ሺህ 250 ኩንታል ስንዴ በየወሩ ድጎማ አድርጎልኝ ስንዴውን ፈጭቼ በተመጣጣኝ ዋጋ ለማህበረሰቡ እንዳስረክብ እገዛ አድረጎልኛል፡፡
ዙራሙሪ፡- ፋብሪካው በቶሎ ወደ ስራ በመግባቱ ያገኝኽው ማበረታቻ እና እውቅና በተመለከተስ ?
አቶ ይስማው፡- በዱቄት ጥራት ፣በኪሎ ጥራት እና በንፅህና የክልሉ ንግድ ቢሮ እውቅና ሰጦኛል፡፡በግብር አከፋፍልና በኢንዱስትሪው ዘርፍ ፈር ቀዳጅ ተብየ በየትኛውም መ/ቤት ቅድሚያ መስተናገድ የምችልበት መታወቂያ ተሰጦኛል፡፡
ዙራሙሪ፡- ስለ ግብር መክፈል ያለህ አመለካክት ?
አቶ ይስማው:- ግብር በመክፈሌ ሰላም አግኝቻለሁ ፣ያፈራሁት ንብረት ተጠብቆልኛል፣መሰረተ ልማቶች በመስፋፋታቸው ተጠቃሚ ነኝ፡፡ስለሆነም ግብር መክፈል ለራስም ለሀገርም ዕድገት ቁልፍ ሚና ይጫወታል፡፡
ዙራሙሪ፡- ወደ እርሻ ስንመለስ ለምን ያህል ሰዎች የስራ ዕድል ፈጥሯል ? ክፍያችውስ ?
አቶ ይስማው፡- ለ7 ቋሚ ለጊዜያዊ ደግሞ እስከ 300 ሰዎች የስራ ዕድል ፈጥሯል፡፡ከቀን ሰራተኛ 100 ቋሚ ሰራተኛ 10 ሺህ ብር እከፍላለሁ፡፡
ዙራሙሪ፡- ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ያለህ አስተዋፅኦ በተመለከተ ድጋፍህ ምን ይመስላል ?
አቶ ይስማው ፡- 110 ሺህ ብር ቦንድ ያለወለድ በእኔ እና በቤተሰቦቼ ስም ገዝቻለሁ፡፡ በቀጣይም ግድቡ እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፌ ይቀጥላል፡፡
ዙራሙሪ፡- ማህበራዊ ህይዎትህ እና ለማህበረሰቡ እያደረግህ ያለው ድጋፍስ ?
አቶ ይስማው፡- በማህበራዊ ህይዎቴ ከሰዎች ጋር ተስማምቼ የምኖር ሰው ስሆን በሀይማኖታዊ ተቋማት ግንባታ የአቅሜን በማድረግ ላይ እገኛለሁ፡፡ሀብት ንብረት ባፈራሁት እሁዲት ከተማ የእኔ ድርሻ 50% የሆነው በ5 ሚሊዮን ብር ግዙፍ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ጓድኞቼን በማስተባበር መገንባት ችያለሁ፡፡ሌላው ከእሁዲት ወደ እርሻው የሚወስደውን 15 ኪ.ሜ የጠጠር መንገድ አሰርቻለሁ፡፡በእንጅባራ ከተማ በአንድ ቤተክርስቲያን ለአዳራሽ ግንባታ 100 ሺህ ብር አስተዋፅኦ አድርጌያለሁ፡፡ በአንከሻ ጓጉሳ ወረዳ በምጠየቅባቸው ልማቶች ሁሉ በግሌና በእርሻው ስም ድጋፍ በማድረግ ላይ እገኛለሁ፡፡በአሁኑ ሰዓት በፋብሪካው ስም አንድ ማየት የተሳነው የዩኒቨርስቲ ተማሪ በየወሩ 1000 ብር በመክፈል በማስተማር ላይ ነኝ፡፡
ዙራሙሪ ፡- የጊዜ አጠቃቅምህ ምን ይመስላል ?
አቶ ይስማው፡- ኑሮህን ለመቀየር አንድ ስራ ብቻ መስራት በቂ አይደለም፡፡እኔ ጊዜን በአግባቡ ነው ምጠቀመው ከፋብሪካውና ከእርሻው ጎን ለጎን ሰሊጥ ከንግዱ ማህበረሰብ በመሰብሰብ በዓመት እስከ 10 ሺህ ኩንታል ለማዕከላዊ ገበያ አቀርባለሁ፡፡ስለሆነም ጊዜን በአግባቡ በመጠቀም ስኬታማ መሆን ይቻላል፡፡
ዙራሙሪ፡- ያንተን ተሞክሮ ለሌሎች በማስተላለፍ ያለህ ልምድ ?
አቶ ይስማው፡- ለእኔ መሰል ነጋዴዎች እና ወደ ንግዱ አለም ለሚቀላቀሉ ግልሰቦች እኔ ያለፍኩትን ወጣ ውረድ እንዲያዩ ምቹ ሁኔታዎችን አሳያቸዋለሁ፡፡ በዚህ አከባቢ ተባብሮ የመስራት ልምድ ዝቅተኛ ነው ድር ቢያብር ነውናተረቱ መረዳዳት ካለ ብዙ ባለሀብቶችን ማፍራት እንችላለን ፡፡ ስለዚህ እኔ በመተባበርና በመተጋገዝ አምናለሁ፡፡ የእኔን ፈለግ በመከተልም አሁን ላይ ፋብሪካ በመገንባት ወደ ምርት ማምረት የገቡ ጓደኞችን ማየት ችያለሁ ፡፡
ዙራሙሪ፡- ስኬታማ ነኝ ማለት ትችላለህ ?ወደ ስኬት የሚያደርሱ ዋና ዋና ነገሮችስ ?
አቶ ይስማው፡- እኔ ስኬታማ ሰው ነኝ ከምንም ተነስቼ አሁን ላይ ጥሩ ህይዎት መኖር ጀምሪያለሁ ለዚህ ደግሞ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፡፡ስኬታማ ለመሆን እምነት፣ ጠንክሮ መስራት እና ትግስት ዋና ዋና መሰረታዊ ነገሮች ናቸው፡፡
ዙራሙሪ፡- ጠቅላላ ካፒታልህ ምን ያህል ደርሷል ? ሀብት ንብረት ?
አቶ ይስማው፡- /ሳቅ/ ጠቅላላ ካፒታሌ እስከ 30 ሚሊዮን ብር ይደርሳል፡፡ 1ተሳቢ፣የቤት መኪና፣3 መኖሪያ ቤቶች በእሁዲት ከተማ 1 መኖሪያ ቤት በእንጅባራ እንዲሁም 1 ሆቴል አለኝ፡፡
ዙራሙሪ፡- ለዚህ መድረስህ ድጋፍ ያደረጉልህ ግለሰቦች ካሉ ?
አቶ ይስማው፡- በዚያ በከሰርኩበት ወቅት አቶ በላይነህ ክንዴ የእኔን ታሪክ በማጥናት ህይዎቴን የቀየረኝ የመጀመሪያው ሰው ነው፡፡ያለኝን ትንሽ ገንዘብ ከባንክ ጋር በማግናኜት እና በእምነት እስከ 1 ሚሊዮን ብር በማበደር ስኬታማ እንድሆን አግዞኛል፡፡
ዙራሙሪ፡- የባሌቤትህ ድጋፍስ ምን ይመስላል ?
አቶ ይስማማው፡- ከባለቤቴ ጋር የተገናኝነው በባዶ ነው፡፡ለእኔ እዚህ መድረስ የሷ ድርሻ ከፍተኛ ነው፡፡
ዙራሙሪ፡- ባለቤትሽን እንዴት ታግዥዋለሽ ? እንዴት ትገልጭዋለሽ ?
ወ/ሮ የተመኝ ታደስ፡- ባለቤቴ ቤተሰቦቹን የሚወድ ፣ጠንካራ ሰው ነው ፣በምችለው ሁሉ አግዘዋ ለሁ፣በፋብሪካው የመቆጣጠር ስራዎች እሰራለሁ፡፡
አቶ ይስማው ከባለቤታቸው ከወ/ሮ የተመኝ ጋር በመኖሪያ ቤታቸው
ዙራሙሪ፡- በጣም የተደሰትክበት ጊዜ እና የአዘንክበት ቀን ካለ ?አቶ ይስማው፡- በህይዎቴ ሁሌም ደስተኛ ነኝ ነገር ግን በጣም የተደሰትኩበት ጊዜ እሁዲት ከተማ ቤተክርስቲያኑ ሲመረቅ ሲሆን ያዘንኩበት ጊዜ ደግሞ ምንም ባልነበረኝ ወቅት የእርሻው አባላት መሬት ተከፋፈለን እንረስ ያሉኝ ግዜ ነው፡፡
ዙራሙሪ፡- አቶ ይስማውን ከዚህ በኃላ በምን በምን ስራዎች ተሰማርቶ እንጠብቀው ?
አቶ ይስማው፡- የቀጣይ እቅዴ ያሰበኩት ፓስታና መኮረኒ ፋብሪካዎች በቅርቡ ለመጀመር ተዘጋጅቻለሁ፡፡
ዙራሙሪ፡- ሽልማቶችን በተመለከተ ?
አቶ ይስማው፡- 3 የወርቅ ዋንጫ ፣2 ሜዳሊያ ከ15 ያላነሱ የምስክር ወረቀቶች በተለያዩ ጊዚያት ከተለያዩ ተቋማት እውቅና ተሰጦኛል፡፡
ዙራሙሪ፡- የዕድሜውን ግማሽ በበረሃ በመዝመት ስኬታማ የሆነው አቶ ይስማው እምነት እና ጠንክሮ መስራት ዋና መገለጫዎቹ ናቸው፡፡የዙረሙሪ መፅሔት የዝግጅት ክፍላችንም የዚህን የልማት አርበኛ የሆነው በብሔረሰብ አስተዳደራችን ግንባር ቀደም ባለሃብቶቻችን መካከል አንዱ ሲሆን በንግዱ ዓለም ለተሰማሩት ሁሉ የህይዎት ተሞክረው እንደሚያስተምር ጥርጥር የለንም ፡፡ስለሆነም መልካሙን ሁሉ እየተመኝንልህ እደግ ተመንደግ እያልን ዝግጅታችንን በዚህ ጨረስን መልካም የስራ ዘመን ይሁንልህ፡፡

No comments:
Post a Comment